ከአቶ ዳውድ እሹሩሩ በስተጀርባ !!

Habtamu Ayalew

ይህ ሰው ‘አቶ ዳውድ ኢብሳ’ “ከህወሓት ጋር የነበረው የፖለቲካ ሽርክና ፈርሶ ለስደት ከተዳረገ በኋላ ያለፉትን 25 ዓመታት ያሳለፈው አስመራ ከተማ ከሜሎቲው ፈሳሽ በስተጀርባ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደ ነበረ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው።

በአገር ውስጥ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረገው መራር ትግል እና መስዋዕትነት የህወሓት ስረ መሰረት ከአራት ኪሎው ቤተ- መንግስት ሲነቀል ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በክብር ከተጋበዙት አንዱ ሆነ።

ይሁን እንጂ የአቶ ዳውድ ነገር “አፈር ሲሉት መሬት፤ መሬት ሲሉት አፈር” ሆነና የክብር ጥሪውን አናንቆ ጥሎ ኦሮሚያን ካልገነጠልኩ እረፍት የለኝም ጦር አነሳለሁ የሚል መግለጫ አወጣ። የዳውድ አንድ ሺህ አምስት መቶ ወታደር እንኳን ከመከላከያ ሰራዊት ከወረዳ ሚሊሻ አቅም ጋር የሚተካከል እንዳልሆነ ቢታወቅም የለውጡ አመራር እራሱን ዝቅ አድርጎ በትዕግስት ተደራደረ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ ልምምጥ ደጅ ጠናው።

ይህ የሆነበት ምክንያት ዳውድ ተስማምቶ ወደ አገር ካልገባ የሚፈጠር ችግር አለ ተብሎ ስለተሰጋ ሳይሆን ሰውዬው በአረመኔው የህወሓት ቡድን በክህደት ከተገፉት አንዱ ነው በሚልና ባመነበት የትግል ጎራ ተሰልፎ ብዙ ዘመኑን በፖለቲካ አለም ስላሳለፈ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነበር። ሌላው በነ አቶ ለማ መገርሳ ኦዴፓ የፖለቲካ ስሌት ኦሮሞን አንድ በማድረግ ኃይል የማሰባሰብ ሂደቱን የተሟላ ለማድረግ ከነበረው ፍላጎት አንፃር ዳውድን አስመራ መተው ጠቃሚ ባለመሆኑ እንደነበረም የታወቀ ነው።

ይሁን እንጂ ዳውድ ፍርቱና ፊቷን ዙራለት በህዝብ ትግልና መስዋዕትነት በመጣ ለውጥ በክብር መጠራቱን በአግባቡ ተገንዝቦ ሊጠቀምበት አልቻለም። ይህ ሰው የኢትዮጵያ ህዝብ “እንደ አንድ ሃሳብ መካሪ እንደ አንድ ልብ ተናጋሪ” ሆኖ በብዙ መከራና መስዋዕትነት ህወሓትን ባያንበረክክ ኖሮ እድል ፈንታው በአስመራ ከተማ ጃጅቶ አስከሬኑ እንኳ የወለጋን አፈር ሳይቀምስ መቅረት እንደነበረ ሊገባው አልቻለም።

የዶክተር አብይ አመራርም ከትዕግስት በላይ በመንዛዛቱ እና በጊዜ ቆራጥ እርምጃ ወስዶ የህግ የበላይነት ባለማስከበሩ እንዲሁም በሌላ በኩል ግልፅ ባልሆነ ህና ከህዝብ በተሰወረ የድርድር አጀንዳ በየጓሮው መማማል አይነት ደካማ ስልት በመከተላቸው ችግሩ እየሰፋ እና ስር እየሰደደ መጥቷል።

አሳዛኙ ነገር አቶ ዳውድ መስዋዕትነት ከፍለው በክብር ወደ አገሩ በማስገባት ያከበሩትን የለውጥ አመራሮች ትቶ ክህደት ፈፅመው በአርጩሜ እየገረፉ ካባረሩት ጋር በመተባበር እና በመመሳጠር አገር ለመበተን ቆርጦ መነሳቱ ነው። አሁን ከዚህ በላይ ማርፈድ ለማንም የማይበጅ ደረጃ ላይ ተደርሷል። የዶክተር አብይ አስተዳደር እንደ አገር ሊቀለበስ ወደማይችል ቀውስ ከመግባታችን በፊት ጥብቅ እርምጃ ወስዶ ይሄን ጋጠ ወጥ ሂደት ሊገታው ይገባል።

መሪው አዲስ አበባ ኢሊሌ ሆቴል ተቀምጦ ከነ አቶ ገምሹ ውስኪ እየጠጣ በእሱ ትዕዛዝ ዜጋ ጭዳ ሲሆን፤ የታጠቀ ኃይል አስማርቶ በግልፅ ወረራ እየፈፀመ ነፃ መሬቴ ነው እያለ ሲቆጣጠር፤ ይህንንም በአደባባይ በሚዲያ ሲያውጅ መንግስት ሁኔታውን ከዚህ በላይ በዝምታ የሚያይበት አንድም ቀሪ ምክንያት የለም።

አንዳንዶች ዳውድ መንግስትን የሚፈታተን ትልቅ ሰራዊት እንዳለው አስመስለው መፃፋቸውም በእጅጉ የተሳሳተ እንደሆነ በሚገባ ባውቅም ዝም ከተባለ የተነገረውን መሆን አይችልም ማለት እንደሆነ መገንዘብ ግን ጥሩ ይመስለኛል።

የስሜን ያህል እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ግን መንግስት ዝምታና ቸልተኛነትን ባይመርጥ ዳውድ አሁን ያለው የታጠቀ ኃይል አንድ ቀበሌ መቆጣጠር የሚችል አይደለም። ዜጋ እየሞተ ወንበዴ በየቀኑ እየተስፋፋ ኔትወርኩን ከመቀሌ ወለጋ ሲያስተሳስር ዝም ማለት ግን መንግስት በሂወት መኖሩን ያስጠረጥራል።

መንግስት ካለ በእርግጥ በሒወት መኖሩን ተንቀሳቅሶ
ለያሳየን ይገባል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.